ማክሰኞ 26 ጃንዋሪ 2016

የጠሉት ይደርሳል የፈሩት ይወርሳል

“የጠላነው የሚደርስበት የፈራነው የሚወርስበት ምክንያት”

በቁሳዊ (ፊዚካል) ሳይንስ ዓለም ውስጥ ተቃራኒ አካላቶች እንደሚሳሳቡ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ በአንፃሩ በስነ ልቡናው ዓለም ተመሳሳይ ነገሮች ይሳሳባሉ የሚል አመለካከት አለ፡፡ በአጭሩ “በሕይወታችን ወጥተን ወርደን የምናገኘው ነገር የሚመስለንን፣ የምንኖረው የምናስበውን፣ የምንሆነው የምንመኘውን ነው” የሚል ፍቺ ነው ያለው፡፡ በአንድ ተራ ቀን ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሀሳቦች ወደ አእምሯችን ጓዳ ይጎርፋሉ፡፡ ከእነዚህ ሀሳቦች ውስጥ ሚዛን የሚደፉት ሀሳቦች ሕይወታችን የያዝነውን መልክ እንዲይዝ መንስኤ ናቸው፡፡ እያልኩ ያለሁት አብዝተን የምናስበውን እንሆናለን ነው፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ የምናስበው ሀሳብ ከተራ ምኞት የዘለለ ወደ ተጨባጭ እውነታነት የሚቀየርበት እድል የሌለው የሕልም ቅቤ ነው፡፡

ወደድንም ጠላንም ሕይወታችን የአስተሳሰባችን ቅኝት ነው፤ ውጪ የምንመለከተው ኑሯችን የማንመለከተው የውስጥ ሀሳባችን ነፀብራቅ ነው፡፡ ፈረንጆቹ “what goes around comes around” ይላሉ፡፡ የሄደ ነገር ተመልሶ መምጣቱ አይቀሬ ነው የሚል ትርጉም አለው፡፡ ሀሳብ ኃይል አለው፤ ጉልበት አለው፡፡ ከውስጣችን ሲፈልቅ፣ ለሌሎች ሲገለፅም ሆነ ለራስ ብቻም ሲታሰብ የሚመስለውን ጠፍጥፎ ሰርቶ ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡ አንድ አንድ ጊዜ በፍርሀት እና ጭንቀት ብቻ ሰዎች አካላቸው የሚመነምነው እንዲሁም ታማሚ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ደስታ ብቻውን ፊታችንን እንደ ጨረቃ የሚያበራውም ለዚህ ነው፡፡ የማይጨበጥ ሀሳብ የሚጨበት ቁስ አካል ይሆናል፡፡ በሀሳብ እና ቁስ መካከል ያለው ልዩነት የመጨበጥ እና ያለመጨበጥ ብቻ ነው፡፡ ከኮምፒውተር ጋር አመሳስለን ብንመለከተው ሀሳብ “ኦፕሬቲንግ ሶፍትዌር” ነው፤ ቁስ አካላት ደግሞ “ሀርድዌር”፡፡ ኮምፒውተሩ የሚሰራው በሶፍትዌሩ ምሪት ነው፡፡ ኮምፒውተሩ ላይ ሰርተን የምናገኘው የትኛውም ነገር ወደ ኮምፒውተሩ ያስገባነው ነገር ውጤት ነው፡፡ “Garbage in garbage out” እንዲሉ፡፡ በጎ ማሰብ በጎ ነገር ወደ ሕይወት ይዞ ሲመጣ ክፉ ሀሳብ ክፉ ክፉውን እንዲሁ ጎትት ይዞ ይመጣል፡፡ እህል ለሰጠ አፈር ወርቅ ለሰጠ ጠጠር መስጠት ሁልጊዜ የሚያጋጥም ክስተት አይደለም፡፡ እህል የሰጠ እህል ወርቅ የሰጠም ወርቅ ነው የሚያገኘው፡፡ መልካም ነገሮች በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙት “የአያቴ ምርቃት እኮ ነው” የሚል ወዳጅ አለኝ፡፡ በልጅነቱ መልካም ልጅ ነበር፡፡ አሁን የሚያጋጥመው መልካም ነገር የዛ መልካም ልጅነት ውጤት ነው፡፡ እዚህ ሀሳብ ውስጥ ቁልፉ ነገር በእርግጥ አስተዳደጉ በጎ አመላከከት እንዲኖረው አድርጓል የሚለው ነው፡፡ ቢያንስ እኔ ይኼንን መመስከር እችላለሁ፡፡

ደግመን ደጋግመን የምናስባቸው ሀሳቦች፣ አእምሮአችን የሚያወጣቸው እና የሚያወርዳቸው ግምቶች እና መላ ምቶች እንዲሁም በዓይነ ህሊናችን መላልሰን የምንቃኛቸው ነገሮች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ወደ ሕይወታችን ነፍስ ዘርተው አካል አውጥተው ይከሰታሉ፡፡ መጥፎ የሕይወት አጋጣሚ የምትሉትን አንድ ነገር እስኪ ለማስታወስ ሞክሩ፡፡ ስራ ማጣት፣ ከሚወዱት ሰው ጋር መለያየት ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ የክስተቱን መነሻ ገመድ ጫፍ ይዛችሁ እስከ ሌላኛቸው ጫፍ ድረስ ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ስትቃኙት በአእምሯችሁ ይፈጠራል ብላችሁ አስቀድማችሁ ያሰባችሁት፣ ውስጣችሁ በስጋት መልኩ የተመላለሰ፣ የጠረጠራችሁት ወዘተ ክስተት ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ “የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል” ማለት ይኼ ነው፡፡ ትልልቅ ፈተናዎች ጎዳናችን ላይ ጋሬጣ ሆነው ሲመጡ ፍርሀት እና ንዴት ውስጣችን ይፈጠራል፡፡ በእርግጥ ይኼ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ፈተና ሲጋረጥብን ፈተናውን የምንመለከትበት መንገድ ግን ለፈተናው እጃችንን እንድንሰጥ ወይንም ደግሞ ከፈተናው ደመና በላይ ከፍ ብለን ፈተናውን እንድናልፈው ያደርገናል፡፡ “ነግሬህ ነበር እኮ፣ ባለፈው እንኳን እንደዚህ እንደዛ ሆኖ፣ ሰውን ማመን ድሮም… ወዘተ” የሚል የማያቋረጥ አስጨናቂ ሀሳብ ማሰብ ያንኑ መላልሰን የምናስበውን እና የምንናገረውን ይወልዳል፡፡ ደስ ሲለንም እንዲያው ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በሮዝ  መነፅር እንመለከታለን፤ ለምናገኘው ሰው በሙሉ በጎዎች እንሆናለን፤ ፍቅራችን ይጨምራል፤ አመስጋኝ ነን፤ ሰዎች ለምን እንደሚከፋቸው ሁሉ ግራ ግብት ሊለን ይችላል፡፡ ቀደም ሲል ሀሳብ ጉልበት አለው ብያችኋለሁ፡፡ በእርግጥ ሕይወታችን ውስጥ ለሚፈጠሩ የረቡም ሆኑ ያልረቡ ነገሮች ብቸኛው ተጠያቂ ሁልጊዜም መሆን አለብን እያልኩ አይደለም፡፡ ሳንፈቅድ ሊጫኑብን፣ ሊያጋጥሙን፣ ልናልፍባቸው ወዘተ የሚችሉ ነገሮች አሉ፡፡

ችግር ተደራርቦባችሁ ሀዘን ውስጥ ወድቃችሁ፣ ድብርት ተጫጭኗችሁ ሳለ አጮልቃችሁ የምታዩበት ትንሽ የተስፋ ቀዳዳ ሲታያችሁ ውስጣችሁ መነቃቃት ይፈራል፣ ጥንካሬያቸሁ ያቆጠቁጣል፡፡ በሂደት ወደነበራችሁበት ጥሩ የስሜት ከፍታ ትመለሳላችሁ፡፡ አሁን ምን ማድረግ እንደምትችሉ አጥርታችሁ ትጀምራላችሁ፡፡ ያሏችሁ አማራጮች ጎላ ጎላ ብለው ይታያችኋል፡፡ “ለካ ይኼንንም ማድረግ እችላለሁ” ማለት ትጀምራላችሁ፡፡ “ምን ነክቶኝ ነው እስከዛሬ ድረስ ዓይኔ ስር ቁጭ ብሎ ያላየሁት” ትሉ ሁሉ ይሆናል፡፡ የነካባችሁ እና የጋረደባችሁ አሉታዊ አስተሳሰባችሁ ነው፡፡ አሉታዊ አስተሳሰብ አሉታዊ ነገሮችን ደርቦ ደራርቦ ይዞ እየመጣ መንገዳችሁን ዘግቶት ነበር፡፡ አዎንታዊ ነገር ማሰብ በሌላ መልኩ ስትጀምሩ ግን ማድረግ የምትችሉት ነገር ይገለጥላችኋል፡፡ የተለየ ነገር ስለመጣ ሳይሆን ዓይነ ህሊናችሁን የጋረደው መጥፎ የሀሳብ ሞራ ስለተገፈፈ ነው፡፡ የነካችሁ አዎንታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ አስተሳሰባችሁን መቀየራችሁ ብቻውን ወደ ሕይወታችሁ ተመልሶ የሚመጣውን ነገር መቀየር ሲጀምር ታስተውላላችሁ፡፡ ሁላችንም ከየት ተነስተን ወደየት እንደመጣን ብናስብ አመዛኙ ድላችንም ሆነ ውድቀታችን ከአመለካከታችን ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

“Stickiness” የሚባል የኢንተርኔቱ ፅንሰ ሀሳብ አለ፡፡ አንድ ድረ ገፅ ምን ያህል በተደጋጋሚ በጎብኚዎች ይጎበኛል የሚለውን የሚገልፅ ሀሳብ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በጎ ነገሮች ሕይወታቸው ውስጥ ያለማቋረጥ የሚመጣላቸው (ወረቀት ከፈለኳት እግር አውጥታ ቢሮዬ ድረስ ትመጣከለች ትላለች አንድ ወዳጄ)፣ ደስታ ከፊታቸው ገፅ ላይ የማይጠፋ፣ ያም ያም ያለ ልዩነት የሚወዳቸው ሰዎች አሉ፡፡ አንድ አንድ ጊዜ “ምን አስነክታው? ምን አስነክቷት? ይሆን” የሚል ጥያቄ እናነሳለን፡፡ ለምን ይኼንን ድረ ገፅ ሰዎች ከሌላው የበለጠ ይጎበኙታል ብሎ እንደመጠየቅ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ማራኪ ምስጢራቸው ከአስተሳሰባቸው ጋር የተጋመደ ነው፡፡ ሰው መልካም እንደሆነ ያስባሉ፤ በራሳቸው ይተማመናሉ፤ ቅን እና ተባባሪ ናቸው፤ ከአይቻልም ይልቅ ይቻላል ማለትን ያዘወትራሉ፤ በጥቅሉ አጠር አድርጌ ስገልፀው በአንድ መደበኛ ቀን ውስጥ የሚያስቡት አብዛኛው ሀሳብ በጎ ነው፡፡ በመሆኑም በጎ ነገር በብዛት ይገጥማቸዋል፤ የጥሩ ነገር ማግኔት ናቸው፤ ከውስጣቸው ወደውጪ የሚንፀባረቀው በጎ ሀሳብ በጎ ነገሮችን መልሶ መላልሶ ወደ ሕይወታቸው ይዞ ይመጣል፡፡ መጪው ጊዜ በጎ አሳቢዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ የሚበረክቱበት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡

ቸር እንሰንብት!

ሠዎች የሚሉት አያጡም

አባትና ልጅ ወደ አንድ አካባቢ ረጀም ጉዞ ለማድረግ አህያቸውን ጭነው ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ ጉዞውን እንደጀመሩ ልጅ በአህያው ላይ ቁጭ ብሎ አባት ደግሞ የአህያዋን ልጓም ይዘው በእግራቸው ይጓዙ ጀምር፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ ግን የልጅን በአህያ ላይ መቀመጥ የአባትን በእግር መጓዝ የተመለከቱ ሰዎች “አባቱ በእግሩ እየሄደ እንዴት ልጁ በአህያ ይሄዳል? ምን ዓይነት ስነ ምግባር የጎደለው ልጅ ነው?” በማለት ቅሬታቸውን እና ትችታቸውን ሰነዘሩ፡፡ ይህንን እንደ ሰሙ አባት እውነትም ስህተት የሰሩ መስሏቸው ልጃቸውን በእግሩ የአህያዋን ልጓም ይዞ እንዲሄድ አድርገው እሳቸው ደግሞ በአህያ ላይ ወጥተው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ አሁን ደግሞ ሰዎች አባት ላይ ትችታቸውን ማዥጎድጎድ ጀመሩ;፡፡ “ምን ዓይነት ጨካኝ አባት ነው? ልጁን በእግሩ እያዳከረ እሱ በአህያ እንዴት ይሄዳል” አሉ፡፡ በዚህም አባት ይደናገጡና ከአህያዋ ላይ በመውረድ እንግዲያውስ ሁለታችንም በእግራችን እንሂድ ተባብለው በእግራቸው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ወደ ሌላ መንደር ሲቃረቡ አሁንም አህያዋን ያለ ምንም ጭነት ተዝናንቶ መሄድ እና የአባትና ልጅን በእግር መጓዝ የተመለከቱ የመንደሩ ሰዎች ሌላ ትችት መሰንዘር ጀምሩ፡፡ “ድሮም ሃብት ያላቸው ሰዎች ችግራቸው ይኼ ነው! እንዴት ያላቸውን ነገር መጠቀም እንዳለባቸው አያውቁም” አሉ፡፡ አሁንም ሰውን ማስደስት እንዳልቻሉ እና ልክ እንዳልሆኑ የተሰማቸው አባት እና ልጅ የሚቀጥለው መንደር ሰው አፍ ላለመግባት ሁለቱም በአህያዋ ላይ ወጥተው መጓዛቸውን ቀጠሉ፡፡ ቀጣዩ መንደር እንደደረሱ ግን አባት እና ልጅ የገጠማቸው አሁንም ሌላ ትችት ነው፡፡ “ምን ዓይነት ጨካኝ ሰዎች ናቸው? አንደበት የላትም ብለው ነው? የእግዜር ፍጥረት ላይ ይታያችሁ እስኪ እንዴት ሁለት ሆነው ጀርባዋ ላይ ተዝናንተው ተቀምጠው ይሄዳሉ አንዳቸውን ከተሸከመች አንሶ ነው” አሉ፡፡ አባት እና ልጅ ተደናግጠው ሁለቱም ከአህያዋ ጀርባ ላይ አፍታ እንኳን ሳይቆዩ ወረዱ፡፡ በየደረሱበት ትችት የገጠማቸው አባት እና ልጅም ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ከተመካከሩ በኋላ ቢያንስ ከዚህ በኋላ የምናገኛቸውን ሰዎች ማስደሰት ይኖርብናል ብለው በማሰብ አህያዋን ተጋግዘው ለሁለት ተሸክመው ጉዟቸውን አሁንም ይቀጥላሉ፡፡ አህያዋን በመሸከማቸው ምክንያት እጅግ ተዳክመው ወደ ሚቀጥለው መንድር ይደርሳሉ፡፡ አህያ የተሸከሙትን የከተማዋን ሰዎች የተመለከቱት ሰዎች ወገባቸውን ይዘው መሳቅ ጀመሩ፡፡ ምን ዓይነት ጅል ሰዎች ናቸው አህያዋ ላይ ተቀምጠው እንደመሄድ እንዴት አህያ ተሸክመው ይጓዛሉ በማለት ተሳለቁባቸው፡፡ አባትና ልጅም ምንም ነገር ቢያደርጉ ከሰው ትችት ማምለጥ እንደማይችሉ እና ሁልጊዜም ቢሆን ሰዎች የሚተቹት ነገር ፈልገው እንደማያጡ ተረድተው ጉዟቸውን እነሱ ባሻቸው መንገድ ቀጠሉ፡፡

እውነትም ሰዎች ምንጊዜም ቢሆን የሚሉት አንድ ነገር አያጡም፡፡ የምታደርጉትን ነገር ቢወዱትም ባይወዱትም፤ ልክ ነው ብለው ቢያስቡም ባያስቡም ፤ ቢመለከታቸውም ባይመለከታቸውም አንድ የሚሉት ነገር አያጡም፡፡ መፍትሄው የገዛ ራስን ህይወት በራስ ፍላጎት መምራት ነው፡፡ የአንተ/የአንቺ ህይወት የተባለበትም ምክንያት ይኼ ነው፤ አንተ/አንቺ በአሻችሁ መንገድ ትመሩት ዘንድ ነው፡፡

ስለዚህ የትኛውም ጥሩ ነው፣ ዋጋ አለው፣ ይበጀኛል ወዘተ ብላችሁ ከልባችሁ እስካመናችሁ ድረስ ሰዎች ምንም ይበሉ ምን ከማድረግ ወደ ኋላ አትበሉ፡፡

“The 7 Habits of Highly Effective people”

የሥኬታማ ሰዎች  7 ልምዶች
“The 7 Habits of Highly Effective people”

ከአስራ አምስት ሚሊዮን ቅጂ በላይ ተሽጧል፤ በሰላሳ ቋንቋዎች ተተርጉሞም ለንባብ በቅቷል፤ በእኛው አማሪኛ ቋንቋም ተተርጉሞ መታተሙንም አውቃለሁ፡፡ ይህ መጽሐፍ “The 7 Habits of Highly Effective people” ይባላል:: “እጅግ በጣም ስኬታማ የሆኑ ሰዎች 7 ልምዶች” ብለን ቃል በቃል እንተርጉመው፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ስቴቨን ኮቬይ ይባላል፡፡ ይህ መጽሐፍ በግለሰብ ደረጃ ብልፅግናን (Personal development) ለመፍጠር እንዲረዱ ታስበው እስከ ዛሬ ድረስ ከተጻፉ መጽሐፍት መካከል ወደር የማይገኝለት ነው፡፡ ካላነበባችሁት እንድታነቡት እመክራለሁ፡፡ ያነበብነውም ደግመን ልናነበው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የዚህ ድንቅ መጽሐፍ ደራሲ ስቴቨን ኮቬይ “ውስጣዊ ድል ከውጫዊ ድል ይበልጣል” ይላል፡፡ እዚህ ምድር ላይ ማግኘት የምንፈልጋቸውን ነገሮች በሙሉ ለማግኘት አስቀድመን ራሳችንን ማሸነፍ፤ የህይወታችን ሾፌር መሆን፤ ውስጣዊ ማንነታችንን መቆጣጠር ወዘተ አለብን ማለት ነው፡፡ “ከተማን ከሚመራ ሰው ይልቅ ራሱን የሚመራ ሰው ይበልጣል” ይላል ጠቢቡ ሰለሞን፡፡ ራስን ማሸነፍ ሌሎች ውጫዊ ነገሮችን የማሸነፊያ ቁልፍ ነው፡፡ በመቀጠል በቅደም ተከተል የምንመለከታቸው 7 ልምዶች ማንኛውም ሰው የግል ህይወቱ መሪ እንዲሆን በእጅጉ የሚያግዙ ናቸው፡፡ አሁን ቦታውን ለእነዚህ ልምዶች ለቀቅ እናድርግ እስኪ፡፡

1. ኃላፊነት ውሰዱ

ጅብ ከሄደ በኋላ የውሻ መጮህ ምንም ውጤት አያመጣም፤ ትርፉ ድካም ነው፡፡ ውጤት የሚያመጣው ጅቡ ከመምጣቱ በፊት አስቀድሞ በማነፍነፍ ድምጽ ማሰማት ነው፡፡ ሁኔታዎችን፣ ሌሎች ሰዎችን፣ ዓለምን ወዘተ የሚወቅሱ ሰዎች በህይወታቸው የረባ ቁም ነገር አያከናውኑም፤ ሁልጊዜም ኃላፊነትን የሚያሸክሙት ከእነሱ ውጪ ላለ ሌላ አካል ነው፡፡ ኃላፊነትን መሸከም ስንችል ነው የህይወታችንን ጉዞ አቅጣጫ መወሰን የምንችለው፡፡ የተሸከርካሪውን መሪ ለሌላ አካል አሳልፈን ሰጥተን የምፈልገው ቦታ አይደለም የደረስኩት፤ በፈለኩት ፍጥነት አይደለም እየተጓዝኩ ያለሁት ወዘተ ልንል አንችልም፤ ብንልም ዋጋ የለውም፡፡ የጉዞውን አቅጣጫ፣ ፍጥነት እና አድራሻ የሚወስነው አሽከርካሪው ነው፡፡ ልምዳችን መውቀስ፣ ጣት መጠቆም፣ ራስን መከላከል ወዘተ ከሆነ እውነቱን ለመናገር የሚወቀስ ነገር ማግኘት አይከብድም፡፡ ዘወትር የእናቴ መቀነት አደናቅፎኝ ነው ማለት ህይወታችን ባለህበት እርገጥ እንዲሆን በር ወለል አድርጎ ይከፍታል፡፡ ስለዚህ ለውጥ ለማምጣት፣ የራሳችን ሰዎች ለመሆን፣ ውስጣችንን ድል ለማድረግ ወዘተ ሁልጊዜም ለገዛ ራሳችን ህይወት ሙሉ ኃላፊነት እንውሰድ፡፡ ቃላችንን የምናከብር፤ በአልንበት ቦታ የምንገኝ፤ በገዛ ራሳችን ጥረት የምንፈልገውን ማንኛውንም ዓይነት ነገር እጃችን ለማስገባት መጓዝ ያለብንን ያህል ርቀት መጓዝ የምንችል ሰዎች እንሁን፡፡ “ስራ እኮ ጠፋ! እኔ ምን ላድርግ?!” ከማለታችን በፊት ስራ ለማግኘት የምንችለውን ድንጋይ በሙሉ መፈንቀላችንን እርግጠኛ እንሁን፤ ቀጣሪዎች የሚፈልጉትን ዕውቀት እና ክህሎት ይዘን ለመገኘት ጥረት እናድርግ፤ የተለመደውንም ያልተለመደውንም አማራጭ እንፈትሽ፡፡ ሳይኮሎጂስቶች “Life is 10 % what happens to us and 90 % how we react to it” ይላሉ፡፡ የህይወታችንን አብዛኛውን (90 %) ክፍል በምንፈልገው መልኩ መስራት እንችላለን ማለት ነው፡፡ የምናጭደው የዘራነውን ነው፡፡

2. የምትፈልጉትን ነገር አስቀድማችሁ እወቁ

ስቴቨን ኮቬይ “ነገሮች ሁለት ጊዜ ይፈጠራሉ” ይላል፡፡ የመጀመሪያው ፈጠራ የሚጠናቀቀው አእምሮአችን ውስጥ ነው፡፡ ከቤት ከመውጣታችን በፊት የምንሄድበትን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ከአንድ እና ሁለት፣ አምስት እና አስር ዓመት ወዘተ በኋላ ምንድን ነው ማግኘት፣ ማድረግ፣ መሆን ወዘተ የምንፈልገው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት ነገሮቹ በተጨባጭም ወደ ህይወታችን የሚመጡበትን ዕድል ከፍ ያደርጋል፡፡ “We rise to the level of our expectations” ይባላል፡፡ የምናገኘው የምናስበውን ነው፤ የምንደርሰው እንደርሳለን ብለን የምናስበው ከፍታ ድረስ ነው፡፡ ግባችንን ማወቃችን ትኩረታችንን ለመሰብሰብ ይረዳናል፤ ከነፈሰው ጋር አንነፍስም፤ በፈተና መካከል ጸንተን እንቆማለን፡፡ ሳይኮሎጂስቶች የህይወታችንን ግብ በቅጡ ለመለየት የሚረዳን አንዱ ሁነኛ መንገድ “የቀብራችን ዕለት እንዲነበብ የምንፈልገውን የህይወት ታሪካችንን መወሰን ነው” ይላሉ፡፡ ቁጭ ብለን ልናስብበት ይገባል፡፡

3. ቅድሚያ ለሚገባቸው ነገሮች ቅድሚያ ስጡ

“ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት” ይባላል፡፡ ቅድሚያ መስጠት ላለብን ነገሮች ቅድሚያ መስጠት አለብን፡፡ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም፡፡ ኮቬይ እንዲህ ይላል፡- “ራሳችሁን ከእነዚህ ሶስት አጉል ልምዶች በአንዱ መውቀስ ቢኖርባችሁ በየትኛው ነው የምትወቅሱት? (1) መስራት ያለብኝን ነገር በቅደም ተከተል መለየት አልችልም፤ (2) በአስቀመጥኩት ቅደም ተከተል መሰረት መስራት አልችልም፤ (3) በወሰንኩት ቅደም ተከተል መሰረት ለመስራት አስፈላጊው ቁርጠኝነት የለኝም፡፡ ብዙ ሰዎች ቁርጠኝነቱ የለኝም ነው የሚሉት፡፡ ጠለቅ ብለን ከመረመርነው ግን እውነቱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እውነቱ ቅደም ተከተሉ ውስጣችን በጥልቀት አለመስረጹ ነው፡፡ ልምድ 2ን ማለትም የህይወት ግባችንን አስቀድመን በሚገባ ለይተን በሚገባ ውስጣችንን መቅረጽ አለመቻላችን ነው”::

4. በጋራ እኩል ተጠቃሚነት መርህ ተመሩ

ከተቃራኒ ፆታ ጀምሮ እስከ የንግድ ስራ ግንኙነት ድረስ በጋራ እኩል ተጠቃሚነት መርህ መመራት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ “አዎ! በሚገባ አምንበታለሁ፡፡ በእኩል ተጠቃሚነት መርህ ነው ህይወቴን የምመራው፡፡” ትሉ ይሆናል፡፡ እንደምትሉት እንደምትኖሩ ግን እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ለማሸነፍ ከመጣር ይልቅ እንዴት በጋራ እኩል ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት አድርጉ፡፡ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን፣ ከሌላው ከፍ ብሎ ለመታየት፣ ልክ ሆኖ ለመገኘት ወዘተ ከመጨነቅ ይልቅ በጋራ እኩል እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ማሰብ እና ይህንን መርህ በየትኛውም የግንኙነታችን መረብ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይበልጥ ውጤታማ ያደርገናል፡፡

5. መጀመሪያ ለመረዳት ጥረት አድርጉ

መጀመሪያ ስንረዳ የሚረዱንን እናገኛለን፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በአንጻሩ ጊዜያችንን የምናጠፋው ሰዎች እንዲረዱን በመፍጨርጨር ነው፡፡ ቆም ብለን  “ምንድነው እስኪ እያሉ ያሉት? ልክ ይሆኑ ይሆን? በየትኛው ማዕዘን ነው እነሱ ጉዳዩን ያዩት?” ወዘተ ብሎ በቀናነት ማሰብ እና ሰዎችን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ሰዎችን የመረዳት ችሎታችን ጥሩ ሲሆን የሚረዱንን ሰዎች ቁጥርም ይጨምራል፡፡

6. 1 + 1 = 3

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ትልቅ መልዕክት ያለው አባባል ነው፡፡ በጋራ የሚሰሩ ስራዎች በግል ከሚሰሩ ስራዎች ይልቅ የላቀ ውጤት ያመጣሉ፡፡ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም፡፡ ሩጫን በመሰለ የግል ጥረትን በከፍተኛ ሁኔታ በሚጠይቅ የውድድር ዘርፍ እንኳን አትሌቶቻችን ሲተባበሩ የሚያስመዘግቡትን አንጸባራቂ ድል እናውቀዋለን፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ በጋራ የመስራትን መንፈስ ማዳበር ጠንካራ ያደርጋል፤ የበዛ ፍሬም ያፈራል፡፡ አብረን መብላት ብቻ ሳይሆን አብረን መስራትንም ባህላችን እናድርግ፡፡ ስቴቨን ኮቬይ እንደሚለው “አንድ ሲደመር አንድ ከሁለት በላይ ነው”፡፡

7. መጋዛችሁን ሳሉ

ስቴቨን ኮቬይ መጽሐፉ ውስጥ ግሩም አፈ ታሪክ አለ፡፡ አንድ ተጓዥ መንገደኛ በአንድ ጫካ ውስጥ አቋርጦ ሲያልፍ አንድ ምስኪን እንጨት ቆራጭ ላቡ ጠፍ እስከሚል ድረስ ያለምንም እረፍት እንጨት ሲቆርጥ ይመለከታል፡፡ ተጓዡ መንገደኛ ቆም ይልና የመጋዙን መደነዝ አስተውሎ ኑሮ “ወዳጄ! ለምን መጋዝህን ዕረፍት ወስድህ አትስለውም?” ይለዋል፡፡ ልፋ ያለው እንጨት ቆራጭ “አይ ለሱ እንኳን ጊዜ የለኝም” የሚል የዋህ ምላሽ ይሰጠዋል፡፡ ይኼ ምስኪን እንጨት ቆራጭ ዕረፍት ወስዶ መጋዙን ቢስል በተሻለ ቅልጥፍና ብዙ እንጨት መቁረጥ እንደሚችል አልተረዳም፡፡

የተራ ቁጥር ሰባት ልምድ መልዕክት ቀላል እና ግልጽ ነው፡፡ በቂ ዕረፍት ምንጊዜም አድርጉ ነው፡፡ ከስራ በኋላ ራሳችሁን ዘና የማድረግ ልምምዱ ይኑራችሁ፡፡ መዝናናት ለጊዜው ከሚሰጠው ደስታ ባሻገር ለቀጣይ ስራ ያዘጋጃል፡፡ ሁልጊዜም እንደምለው ትልልቅ ኩባንያዎች ወጪ ችለው፣ ወርሃዊ ደሞዝ መክፈላቸውን ሳያቋርጡ ሰራተኞቻቸውን የሚያዝናኑት በጣም ቸር ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንም የተዝናና ሰራተኛ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን እና እነሱንም ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡

አንድ አንድ ሰዎች “እኔ መዝናናት አይሆንልኝም” ይላሉ፡፡ “መዝናናት ራሱን የቻለ ችሎታ ነው” ይላል አንድ ሌላ ወዳጄም፡፡ በመሆኑም “እንዴት እንዝናና?” የሚል ጥያቄ ያላችሁ ሰዎች እነዚህን የመዝናኛ አማራጮች እንድትፈትlቸው እጋብዛለሁ፡- ዋና ዋኙ፤ ከወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር አስደሳች ጊዜ አሳልፉ፤ ዮጋ ስሩ፤ ዳንስ ደንሱ፤ ከከተማ ከተቻለም ከሀገርም ወጣ ብላችሁ ጎብኙ፤ ደስታ ይሰጠኛል ብላችሁ የምታስቡትን የትርፍ ጊዜ የመዝናኛ አማራጭን (Hobby) ሞክሩ፡፡

ቸር እንሰንብት!
                         የፅሑፍ ምንጭ  ነጋሽ አበበ

አራቱ ሚሥቶች

__ አራቱ ሚስቶቻችን __

አራት ሚስቶች የነበሩት አንድ ሀብታም ነጋዴ ነበር፡፡ አራተኛ ሚስቱን ከሌሎች አብልጦ በእጅጉ ይወዳታል፡፡ ስለሚወዳትም ጥሩውን ሁሉ ለእርሷ በመስጠት ይንከባከባታል፤ያስደስታታል፡፡ ሦስተኛ ሚስቱን መውደድም ብቻ አደለም ይኮራባታል፣ ይመካባታልም ጭምር፡፡ ይዟት በአደባባይም ለመታየት ይፈልጋል ነገር ግን ጥላው እንዳትሄድ በጣሙን ይሰጋል፡፡ ሁለተኛ ሚስቱንም እንዲሁ ይወዳታል፡፡ ይች ሁለተኛ ሚስቱ በነገሮች አስተዋይና ብልህ ታጋሽም በመሆኗ ይመካባታል፡፡ ነጋዴው አንዳች እክል የገጠመው እንደሁ ችግሩን ታቅፎ እሚያመራው ወደ ሁለተኛ ሚስቱ ነው ፡፡ እሷም በአስቸጋሪው ሰዓት ከጭንቀቱ ትገላግለዋለች፡፡  የመጀመሪያ ሚስቱ በጣም ታማኝ አጋሩ ናት፡፡ ቤቱንና ንግዱን የምትመራለትና የምታስተዳድርለት እሷው ነች፡፡ እሷ በጣም የምታፍቅረው ቢሆንም እሱ ግን ስለማያፈቅራት አንድም ቀን በትውስታው ውስጥ ቦታ ሰጥቷት አያውቅም ነበር፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ህመም ተሰማውና ማለፉን ባሰበ ጊዜ የተድላ ዓለሙን እያስታወሰ እንዲህ አሰበ “አራት ሚስቶችና የተትረፈረፈ ሀብት አለኝ ነግር ግን በሞት ጊዜ ብቻየን እሆናለሁ፡፡ እንዴት ብቻየን እሆናለሁ?” በማለት አራቱንም ሚስቶች በማስጠራት ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡

“ሁላችሁንም በጣም እወዳችኋለሁ:: የሚያምሩ አልባሳትንም እያለበስኩ ሳስጌጣችሁ ኖርኩ፡፡ አሁን ግን ልሞትናውና ከብቸኝነቴ ታድኑኝ ዘንድ ተከተሉኝ” አላቸው፡፡ አራተኛው ሚስቱ “በፍጹም አይሆንም”  ስትል መልሱን ሰጥታው ከአካባቢው ተሰወረች፡፡ ነጋዴው በሰማው ምላሽ ልቡ ተነካ፡፡ ለሦስተኛዋ ሚስቱ  “በሕይዎቴ ሙሉ ስወድሽ ኑሪያለሁ አሁን አብረሽኝ ልትሆኝና ወደምሄድበት  ልትከተይኝ ትፈቅጃለሽ?” አላት በአዘኔታ ሁኖ መልስ ሲጠባበቅ  “አይሆንም ሕይዎት አትጠገብም ፡፡ እዚህ መኖር መልካም ነው፡፡ እናም ከአንተ ሞት በኋላ አግብቸ መኖር እሻለሁ” አለችው፡፡ ይህ ሀብታም ነጋዴ ልቡ ዝቅ ሲልና ወደ ቀዝቃዛነት ሲለወጥ ተሰማው፡፡ አሁንም በተስፋ መቁረጥ ሁኖ “በሕይዎቴ ሙሉ እርዳታን ስፈልግ ወደ አንች ስመላለስ ኑሪያለሁ፡፡ ስትረጅኝም ነበር፡፡ አሁንም እርዳታሽን ፈልጊያለሁና እርጅኝ”  ሲል ሁለተኛ ሚስቱን ጠየቃት፡፡  “በዚህ ሰዓት ልረዳህ ባለመቻሌ አዝናለሁ፡፡ ማድረግ የምችለው አንተን ወደ መቃብርህ መሸኘት ብቻ ነው” ስትለው መብርቅ የመታው  ያህል ክው አለ፡፡ በድንጋጤ ስሜት ተውጦ እያለ  “የትም ብትሄድ እከተልሃለሁ፤ አንተጋ እሆናለሁ!” የሚል ድምጽ ሲያስተጋባ ተሰማው ዓይኑን ሲያነሳ  የተጎሳቆለ እይታ ያላት  የመጀመሪያ ሚስቱ ነበረች ነጋዴው ሳግ እየተናነቀው “ሲኖረኝና ስችል ልንከባከብሽ ይገባኝ ነበረ” በማለት እቅፍ አድርጎ ወደሰውነቱ አስጠጋት፡፡

በመሠረቱ ሁላችንም በሕይዎታችን አራት ሚስቶችን አኑረን ይሆናልና የእኛም ታሪክ ሊሆን ይችላል፡፡

1. አራተኛው ሚስታችን ፈራሹ ስጋችን ነው፡፡ ለምቾቱና ለውበቱ ተጨንቀን ብንደክምም ቀሪ እንጅ ተከትሎን አይሄድም፡፡

2. ሦስተኛው ሚስታችን አለን የምንለው ነገር ንብረት፣ ሀብትና ክብራችን ነው፡፡ ይሄም እኛ ስንሞት ወደሌሎች የሚተላለፍ ነው፡፡

3. ሁለተኛው ሚስታችን ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመናችን የቱንም ያህል ቀረቤታና ቁርኝት ቢኖረንም ማድረግ የሚችሉት እስከ መቃብር መሸኘት ብቻ ነው፡፡

4. የመጀመሪያዎ ሚስታችን ሕያው ነፍሳችን ናት፡፡ ቁስና ሀብት ስናሳድድ ወደ ጎን ገፍተናት ቢሆንም አብራን የምትሆነው እሷው ነችና በመጨረሻው ሰዓት ሳይሆን አሁኑኑ እንድናለመልማት ያስፈልጋል ነው ያታሪኩ ጭብጥ፡፡

ምንጭ፡ The Four wives

ችግሩ

"መርከቡ የተለመደውን ጉዞ እያደረገ ባለበት ሰዓት የኢንጅን ችግር ገጠመውና
ቆመ፡፡
ተቆጣጣሪው የመርከቡን ደህንነት ለመቆጣጠር የተመደቡትን ወጣት
ሙያተኛች ችግሩን
እንዲፈቱት አንድ ባንድ ቢያስሞክርም ምንም መፍትሄ ማምጣት አልቻሉም፡፡
ስለሆነም ከልጅነቱ ጀምሮ በመርከብ ጥገና የኖረና ከፍተኛ ልምድ ያካበተን
ጎልማሳ አስጠሩ፡፡ ጎልማሳውም መሳሪያዎቹን በሻንጣው በሙሉ ሰድሮ ይዞ
መጣና ወደስራ
ተሰማራ፡፡ ከላይ እስከታች እየተዘዋወረም በጥንቃቄ እኢጅኑን ፍተሻ አደረገለት፡፡
ይሄን ሲያድርግ የመርከቡ ተቆጣጣሪ በቅርብ ሆኖ ይመለከተው ነበር፡፡
ሙያውን ተጠቅሞ ችግሩን እንደሚፈታለትም ተስፋ አድርጓል፡፡ ጎልማሳው
ሙያተኛ ከሻንጣው ትንሽ መዶሻ አወጣና ቀስ አድርጎ መታ መታ ሲያደርገው
ኢንጅኑ መስራት ጀመረ፡፡ መዶሻውን ወደ ሻንጣው እየመለሰ “ይሄው ችግሩ
ተፈቶልሀል ወደ ፈለከው ቦታ መሄድ ትችላለህ” አለው
፡፡
ከሳምንት በኃላ የክፍያ ደረሰኝ ተሰርቶ ለመርከቡ ተቆጣጣሪ ደረሰው፡፡
የክፍያው መጠንም አስር ሽ (10,000) ዶላር ይላል፡፡ ሰውየው የሚያየውን
ማመን አልቻለም፡፡ እራሱን ይዞ “ምን ሰርቷልና ነው ይሄን ያህል ክፍያ
መጠየቁ?” ሲል በብስጭት ተናገረና
የዋጋ ዝርዝር እንዲሰራለት ለጎልማሳው መልዕክት ላከ፡፡ የዋጋ ዝርዝሩ ምን
ሊመስል
እንደሚችል ገመታችሁ? ይሄን ይመስል ነበር
• በመዶሻው ለመምታት ሁለት ዶላር (2.00)
• ብልሽቱ የት ላይ ነው የሚለውን ለመለየት ዘጠኝ ሽህ ስምንት መቶ ዘጠና
ስምንት
(9998.00)፡፡ ሲል አስረዳው፡፡"
......
እንግዲህ ኣገሩን የሞላው 'ተቆጣጣሪ' ነው፡፡ የሚያስፈልገን ደሞ እንዲህ
ያለው መርከብ ጠጋኝ፡፡
                          ምንጭ  Misiganaw Gishen

ለፈገግታ

ለፈገግታ
አንድ አዛዉንት ወደ ቤታቸዉ
እየሄዱ መንገድ ላይ ወጣት
ልጅ ያገኙና ''ልጄ በግ
በእንግሊዘኛ ምን ይባላል?"
ብሎ
ጠየቀዉ::
ወጣቱም በግ በእንግሊዘኛ ሺፕ
(sheep) ይባላል:: ነገር
ግን
ብዙ አይነት በጎች አሉ::
ለምሳሌ:-
=>4 ና 5 በጎች አንድ ላይ
ከሆኑ ፍሬድ ሺፕ(friend
ship)
=>ሁለት ወንድና ሴት በጎች
አንድ ላይ ካሉ ሪሌሽን ሺፕ
(relation ship)
=>አንድ ጎበዝ በግ ሁሉንም
ሚዋጋና ምግብም ሲሰጥ
ብቻዉ ሚበላ ከሆነ ዲክታተር
ሺፕ(dictator ship)
=>ዉጭ ሀገር ያለ በግ ስኮላር
ሺፕ(scholar ship)
=>ብዙ በጎች አንድ ላይ
ካመለኩ ፌሎ ሺፕ(fellow
ship)
=>በጎች የተማሩትን በተግባር
ሲሰሩ አፓረንት ሺፕ
(apparent ship)
=>አንድ በግ ሌሎች በጎችን
እየመራ ከሄደ ሊደር ሺፕ
(leader ship) ይባላል ::
:v #dope_robi_wiz_II

ሰኞ 25 ጃንዋሪ 2016

አፈ ታሪክ

አንድ አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ውብ ልዕልት ነበረች አሉ - ሁሉም የሚያደንቃት ናት፡፡ ግን ማንም ላግባሽ ያላት የለም፡፡ ንጉሡ አባቷ ተስፋ በመቁረጥ አፖሎ የተባለው አምላክ ዘንድ ሄደና አማከረው፡፡ አፖሎም፤ ሳይክ (Psyche) ልዕልቲቱ ወደ ተራራ መውጣት አለባት፡፡ የሐዘን ልብስም ትልበስ፡፡ እዚያም ብቻዋን ትተው፡፡ ቀኑ ከመንጋቱ በፊት አንድ እባብ ይመጣል፡፡ ያገኛታል፡፡ ያገባታልም፡፡”
ንጉሱ ታዘዘው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ልዕልቲቱ ባሏን ልታይ ስትጠብቅ ቆየች፡፡
የሞት ያህል በሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ በአሰቃቂ ቅዝቃዜ በድና መጠበቋን ቀጠለች! በመጨረሻ እንቅልፍ ወሰዳት፡፡
ስትነቃ በአንዳች ቆንጆ ቤተ መንግስት ውስጥ ንግሥት ሆና ራሷን አገኘች! በየማታው ባሏ ይመጣል፡፡ ኢሮስ ይባላል፡፡ ይገናኛታል (ፍቅር ይሰራሉ)፡፡ ግን አንድ ቃል ኪዳን አስገብቷታል፡- “ሳይክ፤ የምትፈልጊውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፡፡ ግን ፊቴን መልኬን አታይም፡፡ ሳታይኝ ሙሉ በሙሉ ልታምኚኝ! ይገባል፡፡” ወጣቷ ያላትን ፈፅማ ለረዥም ጊዜ በደስታ ኖረች፡፡
ምቾት አላት፡፡ መወደድ አላት፡፡ ደስተኛ ናት፡፡ በየማታው ከሚጎበኛት ሰው ጋር ፍቅር ይዟታል! ግን አንዳንዴ ከእባብ ጋር የተጋባች የተጋባች ይመስላታል! አንድ ጧት ማለዳ ላይ፤ ባሏ ተኝቶ ሳለ ፋኖሱን ለኮሰችና ባሏን ኢሮስን መልኩን አየችው፡፡ ወደር የሌለው ቁንጅና ያለው ወንድ ነው፡፡ ከጎና ተኝቷል፡፡ የፋኖሱ ብርሃን ቀሰቀሰው፡፡
ያፈቀራት ሴት፤ አንድዬ አደራውን አለማክበሯን አይቶ ኢሮስ ላንዴም ለሁሌም ተሰወረ፡፡ ልዕልቲቱ ባለ በሌለ ኃይሏ ፍቅረኛዋን ዳግም ለመመለስ ስትፍረመረም አፍሮዳይት የተባለች የባሏን እናት አግኝታ ጥፋቷን አምና ለመነቻት፡፡ ከእንግዲህ ብዙ ልትፈፅማቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ አውቃ፣ ተቀብላ ልትኖር ቃል ገባች፡፡
ምራቷ ግን በልዕልት ውበት ቅናት ይዟት ኖሮ፤ የሁለቱን ፍቅረኞች ዳግም መገናኘት ለመቀልበስ/ ለማነቀፍ ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም፡፡ ልዕልት ሳይክ፤ በተቀበለችው የቤት ስራ መሰረት አንድ ሳጥን ከፈተች፡፡ ለካ ያ ሳጥን ከባድ እንቅልፍ የሚያስወስድ አስማታዊ ሚስጥር ኖሮታል፡፡ ድብን አድርጎ እንቅልፍ ወሰዳት፡፡
መቼም ሳይደግስ አይጣላምና ኢሮስ ደግሞ ከባድ ፍቅር ይዞት ኖሮ እጅግ አድርጐ ተፀፅቷል፡፡ እንደምንም ብሎ ወደ ቤተመንግስቱ ህንፃ ገብቶ ሚስቱን በቀስቱ ጫፍ ጭሮ ቀሰቀሳት፡፡ “በማወቅ ጉጉትሽ ምክንያት ሞት አፋፍ ደርሰሽ ተመለስሽ” አላት፡፡ ዕውቀት ስር መጠለል ሽተሽ ግንኙነታችንን ገሥሠሽ አጠፋሽ! ቃልኪዳንሽን ሰበርሽ! ሆኖም በፍቅር ዓለም ምንም ነገር ለዘለዓለም አይጠፋም፡፡
ባልና ሚስቱ በዚህ ዕምነት ተይዘው/ተጠርንፈው ወደ ዚዑስ ሄዱ፡፡ ፍቅራቸው ከእንግዲህ እንዳይጠፋ ለመኑ፡፡ ዚዑስ ከብዙ ክርክርና ሙግት በኋላ የአፍሮዳይትን ምክር አገኘ፡፡ ከዚያን ቀን ወዲህ ሳይክ (የአንጎላችን አላዋቂ (unconscious) ግን አመክኖአዊ ወገን) እና ኢሮስ (ፍቅር) በደስታና በተድላ ለዘለዓለም ኖሩ!”
በዚህ ታሪክ መሰረት፤ “ይህንን የማይቀበሉና አስማታዊና ሚስጥራዊ ለሆነው የሰው - ልጅ ግንኙነት ማብራሪያ ለማግኘት የሚሹ ሁሉ፤ እንደሳይክ የህይወትን ምርጥ ክፍል ያጣሉ!” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ሳይክ፤ በሆዷ እንዲህ አለች፡-
“አንድ ቀን ቤተ መንግሥት ውስጥ እነቃለሁ! የምፈልገው አንድ ነገር፤ ጊዜ ብቻ ነው!”
*          *          *
በዓለማዊው ህይወታችን ሳያዩ ማመን ከባድ ነው፡፡ ባሌ እባብ ሊሆን ይችላል ብሎ መኖርም ከባድ ነው! እርግጥ፤ “አንድ ቀን ቤተ መንግሥት ውስጥ እነቃለሁ” ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ ግን ድካም አለበት፡፡ በቀስት ተጭሮ እንደመንቃት ቀላል አይደለም፡፡ ቃልኪዳንን መጠበቁን ይጠይቃል፡፡ ለማወቅ ጉጉት ለከት ማበጀትም ይፈታተናል፡፡ በልጦ መገኘትን ጠንቅቆ መቻል እንደው ያለጥረት የሚገኝ፣ ክብሪት እንደመጫርም የቀለለ፣ የዘፈቀደ ነገር አይደለም፡፡ በሀገራችን ተፎካካሪን በልጦ መገኘት እጅግ አዳጋች፣ የቋጥኛማ ተራራ ያህል የማይዘለቅ ችግር ሆኖ ከቆየ ሰነባብቷል፡፡ አንድ ፀሃፊ እንዳለው፤ “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ ዘውድ በኪሱ ይዞ ስለሚዞር “ውይይቱም፣ ድርድሩም፣ ፉክክሩም ሌላውን በማጥፋት ወይም በመጥለፍ ላይ የተመሰረተ ይሆንና ጤናማ ጉዞ አይሆንም፡፡ ጥንትም እንደዚያው ነበር፤ አሁንም ቅኝቱን አልቀየረም፡፡ በዚህ ቅኝት ላይ የመከፋፈል ዜማ ሲጨመርበት ለባላንጣ ሲሳይ የመሆን አባዜ ይከተላል፡፡ ማ ለምን ይህን አደረገ? ምን እየተጠቀመብኝ ነው? ብሎ ማሰብ ያባት ነው!
ተፈጥሮውን ማሳየት የሚበጀው / የሚያዋጣው አንዳንዴ ብቻ ነው፡፡ ከተቻለ ቃናውን ዝቅ ማድረግ መማር አለብህ… ስትጀምር ብዙ ሳትጮህ መጀመር ነው፤ አዋጪው፡፡ የውድድር ዘዴ! “ከጥበብ ሁሉ ከባዱ ደደብነትህን መቼ እንደምትጠቀምበት ማወቅ ነው!” ይላሉ አዋቂ ፀሀፍት፡፡ ብዙ ከመንጫጫት፣ ሰብሰብ ብሎ የማሰብ፣ የማስተዋል ክህሎት ሊኖር ይገባል፡፡ ከተመክሮ ሁሉ ጥንቃቄን የሚፈልግ ተመክሮ የትግል ተመክሮ ነው፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ ጊዜ ኖሮ በቂ ዝግጅት ማጣት አንድም ንዝህላልነት፣ አንድም አቅለ-ቢስ መሆን ነው ከማለት በስተቀር ምን ትርጓሜ ይኖረዋል? ራስን ለክፍፍል ማጋለጥ፣ የራስን ችግር ራስ አለመፍታት፣ የተፎካካሪን ስልትና ስትራቴጂ አለማስላት፣ የህዝብንና የሀገርን ፍላጐት አለማስቀደም፣ የመንገዶችን ኮረኮንችና ሊሾነት አለመለየት አባዜዎች ሁሌ እንደተፈታተኑን አሉ፡፡ ጠንካራነትን ብቻ ሳይሆን ደካማነትንም መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡
”ደካማ ከሆንክ በማታሸንፈው ጦርነት ውስጥ ለክብርህ ብለህ አትዋጋ፡፡ ይልቁንም ማፈግፈግን እወቅ፡፡ ማፈግፈግ ጊዜ መግዛት ነው፡፡ ማገገሚያ ነው፡፡ ቁስልህን ማከሚያና ባላንጣህን ማዳከሚያ ነው፡፡ ቁልፉ ነገር ማፈግፈግን የኅይል ማፍሪያ መሳሪያ ማድረጉ ነው!”
ጉዞን በረዥሙ ማቀድ ሌላው የብልህነት ስልት ነው፡፡ “ዛሬ ካልተሳካ ሞቼ እገኛለሁ” ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው! አጓጉል ፍዘትም ስስ ብልት መስጠት ነው፡፡ ፖለቲካ ማመዛዘንን፣ ጊዜ-መግዛትንና ፍጥነትን መሰረት የሚያደርግ “ሸቃባ ሚዛን” ነው ይባላል፡፡ ይሄን ልብ ማለት ግድ ነው፡፡ “ታሪክ ባሸናፊዎች የሚፃፍ ተረት ነው!” የሚባለውንም አለመርሳት ነው፡፡
ታዲያ ፀጋዬ ገ/መድህን በሼክስፒሩ ሐምሌት እንደሚለን፡-
“…ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም
አንዴ ከገባህበት ግን እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም”
የሚለውን ሳንዘነጋ ነው፡፡ ሁሉም መስዋእትነት ይጠይቃል፡፡ መስዋእትነት እንደ ዴሞክራሲ ሁሉ ገጠመኝ አይደለም፡፡ ቀድመው መሰረትና እሳቤ የሚያበጁለት ነው፡፡
“አንተኛም ካላችሁ እንገንድሰው
መኝታ እንደሆነ ቀርቷል ካንድ ሰው!” እያልን የምናላዝንበትም ከቶ አይደለም፡፡ ሂደት ነው፡፡ መቀጠል አለበት፡፡ ዝምታ እንኳ መስዋእትነት የሚጠይቅበት ጊዜ አለ፡፡ ትግል በጥበብ የተሞላ መንገድ ነው! ካልበሰሉ በድፍረት ብቻ የሚወጡት የወጣት ስሜታዊነት ዘመቻ መሆኑ ቀርቷል፡፡ እንደ ፋሽን በወረት የሚያሸበርቁበት የገና ዛፍም አይደለም፡፡ ከጀመሩ በኋላ “ፉርሽ ባትሉኝ!” የሚባልበት ጨዋታም አይደለም! “ሰይ ብል ባንከረባብት” እያሉ ያሹትን የሚያጭዱበት ቁማርም መሆን የለበትም! “አርፋ ስጠኝ”፣ “አቫንስ ስጠኝ” እያሉ የሚጠባበቁበት አይደለም፡፡ ትግል መሰረቱ የፖለቲካ ክህሎት ነው፡፡ ያልተነገረ ያልተሰማ ነገር የለም፡፡ ከአንጃ እስከ ዋና መስመር፣ ከቀኝና ግራ መንገደኛ እስከ አምስተኛ-ረድፈኛ፣ ከውጪ ወራሪ እስከ ውስጥ ቦርቧሪ፣ ከአናርኪስት እስከ ዘውድ-ናፋቂ፣ ከገንጣይ-አስገንጣይ እስከ በታኝ-ከፋፋይ፣ ከጠባብ እስከ ትምክህተኛ፣ ከአኢወማ እስከ ሊግ፣ ከአንጋፋው ፎረም እስከ ብላቴናው ፎረም…” ስርዝ የኔ ድልዝ ያንተ፣ እመጫት የሷ፣ ሆያ-ሆዬ የሰፊው ህዝብ ስንባባል በኖርንበት አገር ትግል “ሁለት አንድ ዐይናዎች ተጋብተው ሁለት ዐይን ያለው ልጅ ወለዱ፡፡ ምነው ቢሉ፣ አንዱን ከእናቱ አንዱን ከአባቱ!” ብለው የሚገላገሉት አይደለም!? “ዋና የማይችል ባህር አይግባ፤ ትግል የማይችል ልፊያ አይውደድ” የሚባለው ተወዶ አይደለም፡፡ እሙናዊውን ዓለም እናጢን! ሁሌ ልጅ አንሁት - ልብ-እንግዛ!!