ማክሰኞ 26 ጃንዋሪ 2016

ሠዎች የሚሉት አያጡም

አባትና ልጅ ወደ አንድ አካባቢ ረጀም ጉዞ ለማድረግ አህያቸውን ጭነው ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ ጉዞውን እንደጀመሩ ልጅ በአህያው ላይ ቁጭ ብሎ አባት ደግሞ የአህያዋን ልጓም ይዘው በእግራቸው ይጓዙ ጀምር፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ ግን የልጅን በአህያ ላይ መቀመጥ የአባትን በእግር መጓዝ የተመለከቱ ሰዎች “አባቱ በእግሩ እየሄደ እንዴት ልጁ በአህያ ይሄዳል? ምን ዓይነት ስነ ምግባር የጎደለው ልጅ ነው?” በማለት ቅሬታቸውን እና ትችታቸውን ሰነዘሩ፡፡ ይህንን እንደ ሰሙ አባት እውነትም ስህተት የሰሩ መስሏቸው ልጃቸውን በእግሩ የአህያዋን ልጓም ይዞ እንዲሄድ አድርገው እሳቸው ደግሞ በአህያ ላይ ወጥተው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ አሁን ደግሞ ሰዎች አባት ላይ ትችታቸውን ማዥጎድጎድ ጀመሩ;፡፡ “ምን ዓይነት ጨካኝ አባት ነው? ልጁን በእግሩ እያዳከረ እሱ በአህያ እንዴት ይሄዳል” አሉ፡፡ በዚህም አባት ይደናገጡና ከአህያዋ ላይ በመውረድ እንግዲያውስ ሁለታችንም በእግራችን እንሂድ ተባብለው በእግራቸው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ወደ ሌላ መንደር ሲቃረቡ አሁንም አህያዋን ያለ ምንም ጭነት ተዝናንቶ መሄድ እና የአባትና ልጅን በእግር መጓዝ የተመለከቱ የመንደሩ ሰዎች ሌላ ትችት መሰንዘር ጀምሩ፡፡ “ድሮም ሃብት ያላቸው ሰዎች ችግራቸው ይኼ ነው! እንዴት ያላቸውን ነገር መጠቀም እንዳለባቸው አያውቁም” አሉ፡፡ አሁንም ሰውን ማስደስት እንዳልቻሉ እና ልክ እንዳልሆኑ የተሰማቸው አባት እና ልጅ የሚቀጥለው መንደር ሰው አፍ ላለመግባት ሁለቱም በአህያዋ ላይ ወጥተው መጓዛቸውን ቀጠሉ፡፡ ቀጣዩ መንደር እንደደረሱ ግን አባት እና ልጅ የገጠማቸው አሁንም ሌላ ትችት ነው፡፡ “ምን ዓይነት ጨካኝ ሰዎች ናቸው? አንደበት የላትም ብለው ነው? የእግዜር ፍጥረት ላይ ይታያችሁ እስኪ እንዴት ሁለት ሆነው ጀርባዋ ላይ ተዝናንተው ተቀምጠው ይሄዳሉ አንዳቸውን ከተሸከመች አንሶ ነው” አሉ፡፡ አባት እና ልጅ ተደናግጠው ሁለቱም ከአህያዋ ጀርባ ላይ አፍታ እንኳን ሳይቆዩ ወረዱ፡፡ በየደረሱበት ትችት የገጠማቸው አባት እና ልጅም ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ከተመካከሩ በኋላ ቢያንስ ከዚህ በኋላ የምናገኛቸውን ሰዎች ማስደሰት ይኖርብናል ብለው በማሰብ አህያዋን ተጋግዘው ለሁለት ተሸክመው ጉዟቸውን አሁንም ይቀጥላሉ፡፡ አህያዋን በመሸከማቸው ምክንያት እጅግ ተዳክመው ወደ ሚቀጥለው መንድር ይደርሳሉ፡፡ አህያ የተሸከሙትን የከተማዋን ሰዎች የተመለከቱት ሰዎች ወገባቸውን ይዘው መሳቅ ጀመሩ፡፡ ምን ዓይነት ጅል ሰዎች ናቸው አህያዋ ላይ ተቀምጠው እንደመሄድ እንዴት አህያ ተሸክመው ይጓዛሉ በማለት ተሳለቁባቸው፡፡ አባትና ልጅም ምንም ነገር ቢያደርጉ ከሰው ትችት ማምለጥ እንደማይችሉ እና ሁልጊዜም ቢሆን ሰዎች የሚተቹት ነገር ፈልገው እንደማያጡ ተረድተው ጉዟቸውን እነሱ ባሻቸው መንገድ ቀጠሉ፡፡

እውነትም ሰዎች ምንጊዜም ቢሆን የሚሉት አንድ ነገር አያጡም፡፡ የምታደርጉትን ነገር ቢወዱትም ባይወዱትም፤ ልክ ነው ብለው ቢያስቡም ባያስቡም ፤ ቢመለከታቸውም ባይመለከታቸውም አንድ የሚሉት ነገር አያጡም፡፡ መፍትሄው የገዛ ራስን ህይወት በራስ ፍላጎት መምራት ነው፡፡ የአንተ/የአንቺ ህይወት የተባለበትም ምክንያት ይኼ ነው፤ አንተ/አንቺ በአሻችሁ መንገድ ትመሩት ዘንድ ነው፡፡

ስለዚህ የትኛውም ጥሩ ነው፣ ዋጋ አለው፣ ይበጀኛል ወዘተ ብላችሁ ከልባችሁ እስካመናችሁ ድረስ ሰዎች ምንም ይበሉ ምን ከማድረግ ወደ ኋላ አትበሉ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ