“የጠላነው የሚደርስበት የፈራነው የሚወርስበት ምክንያት”
በቁሳዊ (ፊዚካል) ሳይንስ ዓለም ውስጥ ተቃራኒ አካላቶች እንደሚሳሳቡ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ በአንፃሩ በስነ ልቡናው ዓለም ተመሳሳይ ነገሮች ይሳሳባሉ የሚል አመለካከት አለ፡፡ በአጭሩ “በሕይወታችን ወጥተን ወርደን የምናገኘው ነገር የሚመስለንን፣ የምንኖረው የምናስበውን፣ የምንሆነው የምንመኘውን ነው” የሚል ፍቺ ነው ያለው፡፡ በአንድ ተራ ቀን ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሀሳቦች ወደ አእምሯችን ጓዳ ይጎርፋሉ፡፡ ከእነዚህ ሀሳቦች ውስጥ ሚዛን የሚደፉት ሀሳቦች ሕይወታችን የያዝነውን መልክ እንዲይዝ መንስኤ ናቸው፡፡ እያልኩ ያለሁት አብዝተን የምናስበውን እንሆናለን ነው፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ የምናስበው ሀሳብ ከተራ ምኞት የዘለለ ወደ ተጨባጭ እውነታነት የሚቀየርበት እድል የሌለው የሕልም ቅቤ ነው፡፡
ወደድንም ጠላንም ሕይወታችን የአስተሳሰባችን ቅኝት ነው፤ ውጪ የምንመለከተው ኑሯችን የማንመለከተው የውስጥ ሀሳባችን ነፀብራቅ ነው፡፡ ፈረንጆቹ “what goes around comes around” ይላሉ፡፡ የሄደ ነገር ተመልሶ መምጣቱ አይቀሬ ነው የሚል ትርጉም አለው፡፡ ሀሳብ ኃይል አለው፤ ጉልበት አለው፡፡ ከውስጣችን ሲፈልቅ፣ ለሌሎች ሲገለፅም ሆነ ለራስ ብቻም ሲታሰብ የሚመስለውን ጠፍጥፎ ሰርቶ ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡ አንድ አንድ ጊዜ በፍርሀት እና ጭንቀት ብቻ ሰዎች አካላቸው የሚመነምነው እንዲሁም ታማሚ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ደስታ ብቻውን ፊታችንን እንደ ጨረቃ የሚያበራውም ለዚህ ነው፡፡ የማይጨበጥ ሀሳብ የሚጨበት ቁስ አካል ይሆናል፡፡ በሀሳብ እና ቁስ መካከል ያለው ልዩነት የመጨበጥ እና ያለመጨበጥ ብቻ ነው፡፡ ከኮምፒውተር ጋር አመሳስለን ብንመለከተው ሀሳብ “ኦፕሬቲንግ ሶፍትዌር” ነው፤ ቁስ አካላት ደግሞ “ሀርድዌር”፡፡ ኮምፒውተሩ የሚሰራው በሶፍትዌሩ ምሪት ነው፡፡ ኮምፒውተሩ ላይ ሰርተን የምናገኘው የትኛውም ነገር ወደ ኮምፒውተሩ ያስገባነው ነገር ውጤት ነው፡፡ “Garbage in garbage out” እንዲሉ፡፡ በጎ ማሰብ በጎ ነገር ወደ ሕይወት ይዞ ሲመጣ ክፉ ሀሳብ ክፉ ክፉውን እንዲሁ ጎትት ይዞ ይመጣል፡፡ እህል ለሰጠ አፈር ወርቅ ለሰጠ ጠጠር መስጠት ሁልጊዜ የሚያጋጥም ክስተት አይደለም፡፡ እህል የሰጠ እህል ወርቅ የሰጠም ወርቅ ነው የሚያገኘው፡፡ መልካም ነገሮች በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙት “የአያቴ ምርቃት እኮ ነው” የሚል ወዳጅ አለኝ፡፡ በልጅነቱ መልካም ልጅ ነበር፡፡ አሁን የሚያጋጥመው መልካም ነገር የዛ መልካም ልጅነት ውጤት ነው፡፡ እዚህ ሀሳብ ውስጥ ቁልፉ ነገር በእርግጥ አስተዳደጉ በጎ አመላከከት እንዲኖረው አድርጓል የሚለው ነው፡፡ ቢያንስ እኔ ይኼንን መመስከር እችላለሁ፡፡
ደግመን ደጋግመን የምናስባቸው ሀሳቦች፣ አእምሮአችን የሚያወጣቸው እና የሚያወርዳቸው ግምቶች እና መላ ምቶች እንዲሁም በዓይነ ህሊናችን መላልሰን የምንቃኛቸው ነገሮች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ወደ ሕይወታችን ነፍስ ዘርተው አካል አውጥተው ይከሰታሉ፡፡ መጥፎ የሕይወት አጋጣሚ የምትሉትን አንድ ነገር እስኪ ለማስታወስ ሞክሩ፡፡ ስራ ማጣት፣ ከሚወዱት ሰው ጋር መለያየት ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ የክስተቱን መነሻ ገመድ ጫፍ ይዛችሁ እስከ ሌላኛቸው ጫፍ ድረስ ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ስትቃኙት በአእምሯችሁ ይፈጠራል ብላችሁ አስቀድማችሁ ያሰባችሁት፣ ውስጣችሁ በስጋት መልኩ የተመላለሰ፣ የጠረጠራችሁት ወዘተ ክስተት ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ “የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል” ማለት ይኼ ነው፡፡ ትልልቅ ፈተናዎች ጎዳናችን ላይ ጋሬጣ ሆነው ሲመጡ ፍርሀት እና ንዴት ውስጣችን ይፈጠራል፡፡ በእርግጥ ይኼ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ፈተና ሲጋረጥብን ፈተናውን የምንመለከትበት መንገድ ግን ለፈተናው እጃችንን እንድንሰጥ ወይንም ደግሞ ከፈተናው ደመና በላይ ከፍ ብለን ፈተናውን እንድናልፈው ያደርገናል፡፡ “ነግሬህ ነበር እኮ፣ ባለፈው እንኳን እንደዚህ እንደዛ ሆኖ፣ ሰውን ማመን ድሮም… ወዘተ” የሚል የማያቋረጥ አስጨናቂ ሀሳብ ማሰብ ያንኑ መላልሰን የምናስበውን እና የምንናገረውን ይወልዳል፡፡ ደስ ሲለንም እንዲያው ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በሮዝ መነፅር እንመለከታለን፤ ለምናገኘው ሰው በሙሉ በጎዎች እንሆናለን፤ ፍቅራችን ይጨምራል፤ አመስጋኝ ነን፤ ሰዎች ለምን እንደሚከፋቸው ሁሉ ግራ ግብት ሊለን ይችላል፡፡ ቀደም ሲል ሀሳብ ጉልበት አለው ብያችኋለሁ፡፡ በእርግጥ ሕይወታችን ውስጥ ለሚፈጠሩ የረቡም ሆኑ ያልረቡ ነገሮች ብቸኛው ተጠያቂ ሁልጊዜም መሆን አለብን እያልኩ አይደለም፡፡ ሳንፈቅድ ሊጫኑብን፣ ሊያጋጥሙን፣ ልናልፍባቸው ወዘተ የሚችሉ ነገሮች አሉ፡፡
ችግር ተደራርቦባችሁ ሀዘን ውስጥ ወድቃችሁ፣ ድብርት ተጫጭኗችሁ ሳለ አጮልቃችሁ የምታዩበት ትንሽ የተስፋ ቀዳዳ ሲታያችሁ ውስጣችሁ መነቃቃት ይፈራል፣ ጥንካሬያቸሁ ያቆጠቁጣል፡፡ በሂደት ወደነበራችሁበት ጥሩ የስሜት ከፍታ ትመለሳላችሁ፡፡ አሁን ምን ማድረግ እንደምትችሉ አጥርታችሁ ትጀምራላችሁ፡፡ ያሏችሁ አማራጮች ጎላ ጎላ ብለው ይታያችኋል፡፡ “ለካ ይኼንንም ማድረግ እችላለሁ” ማለት ትጀምራላችሁ፡፡ “ምን ነክቶኝ ነው እስከዛሬ ድረስ ዓይኔ ስር ቁጭ ብሎ ያላየሁት” ትሉ ሁሉ ይሆናል፡፡ የነካባችሁ እና የጋረደባችሁ አሉታዊ አስተሳሰባችሁ ነው፡፡ አሉታዊ አስተሳሰብ አሉታዊ ነገሮችን ደርቦ ደራርቦ ይዞ እየመጣ መንገዳችሁን ዘግቶት ነበር፡፡ አዎንታዊ ነገር ማሰብ በሌላ መልኩ ስትጀምሩ ግን ማድረግ የምትችሉት ነገር ይገለጥላችኋል፡፡ የተለየ ነገር ስለመጣ ሳይሆን ዓይነ ህሊናችሁን የጋረደው መጥፎ የሀሳብ ሞራ ስለተገፈፈ ነው፡፡ የነካችሁ አዎንታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ አስተሳሰባችሁን መቀየራችሁ ብቻውን ወደ ሕይወታችሁ ተመልሶ የሚመጣውን ነገር መቀየር ሲጀምር ታስተውላላችሁ፡፡ ሁላችንም ከየት ተነስተን ወደየት እንደመጣን ብናስብ አመዛኙ ድላችንም ሆነ ውድቀታችን ከአመለካከታችን ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
“Stickiness” የሚባል የኢንተርኔቱ ፅንሰ ሀሳብ አለ፡፡ አንድ ድረ ገፅ ምን ያህል በተደጋጋሚ በጎብኚዎች ይጎበኛል የሚለውን የሚገልፅ ሀሳብ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በጎ ነገሮች ሕይወታቸው ውስጥ ያለማቋረጥ የሚመጣላቸው (ወረቀት ከፈለኳት እግር አውጥታ ቢሮዬ ድረስ ትመጣከለች ትላለች አንድ ወዳጄ)፣ ደስታ ከፊታቸው ገፅ ላይ የማይጠፋ፣ ያም ያም ያለ ልዩነት የሚወዳቸው ሰዎች አሉ፡፡ አንድ አንድ ጊዜ “ምን አስነክታው? ምን አስነክቷት? ይሆን” የሚል ጥያቄ እናነሳለን፡፡ ለምን ይኼንን ድረ ገፅ ሰዎች ከሌላው የበለጠ ይጎበኙታል ብሎ እንደመጠየቅ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ማራኪ ምስጢራቸው ከአስተሳሰባቸው ጋር የተጋመደ ነው፡፡ ሰው መልካም እንደሆነ ያስባሉ፤ በራሳቸው ይተማመናሉ፤ ቅን እና ተባባሪ ናቸው፤ ከአይቻልም ይልቅ ይቻላል ማለትን ያዘወትራሉ፤ በጥቅሉ አጠር አድርጌ ስገልፀው በአንድ መደበኛ ቀን ውስጥ የሚያስቡት አብዛኛው ሀሳብ በጎ ነው፡፡ በመሆኑም በጎ ነገር በብዛት ይገጥማቸዋል፤ የጥሩ ነገር ማግኔት ናቸው፤ ከውስጣቸው ወደውጪ የሚንፀባረቀው በጎ ሀሳብ በጎ ነገሮችን መልሶ መላልሶ ወደ ሕይወታቸው ይዞ ይመጣል፡፡ መጪው ጊዜ በጎ አሳቢዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ የሚበረክቱበት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡
ቸር እንሰንብት!